ፖለቲካዊ ስርዓት

ስዊዘርላንድ ውስጥ ፖለቲካዊ ስልጣን በሶስት ይከፈላል፣ ፌደራል፣ ካንቶኖች (አባል አገሮች) እና የአካባቢ አስተዳደሮች። ስዊዘርላንዳውያን በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።

የስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ግዛት

የስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ግዛት የተመሰረተው ከ1848 ጀምሮ ነው። ዋና ከተማውም በርን ነው። የስዊዘርላንድ አንድነት በዘር፣ በቋንቋ ወይም በሃይማኖት የተመሰረተ አይደለም። የተለያዩ ባህሎች በነጻ ፍቃዳቸው ነው አንድ የሆኑት። በዚህ ምክንያት ነው „በበጎ ፍቃድ የተመሰረተ ሃገር“ (Willensnation). ተብሎ የሚጠራው።

ፌደራላዊ

በስዊዘርላንድ ውስጥ ያሉት 26 ካንቶኖች እና ከ 2000 በላይ የሚሆኑት ኮሚዩኖች በፖለቲካ ራሳቸውን የቻሉና ነጻ ተቋማት ናቸው። ፌደራላዊ ናቸው የሚባሉትም በዚህም ምክንያት ነው ። እያንዳንዱ ካንቶን እና እያንዳንዱ ኮሚዩን ራሱን የቻለ የክልል መዋቅር አለው። የBasel-Stadt ካንቶን የራሱ ህገ መንግስትና መንግስት፣ ፓርላማ፣ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች አሉት። ኮሚዩኖቹና ካንቶኖቹ ለብዙ መንግስታዊ ጉዳዮች ሃላፊነት ይወጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የትምህርት ቤት ስርዓት ከካንቶን ወደ ካንቶን የተለየ አሰራር ያላቸው በዚህ ምክንያት ነው። ፌደራላዊ ህጎቹ በመላው ስዊዘርላንድ ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ካንቶን የራሱ የሆኑ ህጎች አሉት። የካንቶኑ ህጎችም በካንቶኑ ግዛት ብቻ ነው ተፈጻሚ የሚሆኑት። እያንዳንዱ ኮሚዩን የራሱን ህግ ማጽደቅ ይችላል። ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ፌደራሉ፣ ካንቶኖቹና ኮሚዩኖቹ ቀረጥ/ታክስ ያስከፍላሉ።

የስልጣን ክፍፍል

የፖለቲካ ስልጣን ጥቂት ሰዎች ላይና ጥቂት ተቋማት ላይ ብቻ መጠቅለል ስለሌለበት፣ ስለዚህም ነው የመንግስት ስልጣን በስዊዘርላንድ መንግስት አስተዳደርና በካንቶኖቹ ውስጥ ራሳቸውን የቻሉ ስልጣን ያላቸው ሶስት ተቋማት ይከፈላል። እነሱም ህግ አውጪ አካል (gesetzgebende Gewalt) ፣ ህግ አስፈጻሚ አካልና (gesetzesausführende Gewalt) የዳኝነት አካል (richterliche Gewalt). ናቸው። በካንቶን Basel-Stadt ውስጥ እነዚህን የስራ ተግባራት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሶስቱ ጽ/ቤቶች በሃላፊነት ያከናውናሉ።

  • ህግ አውጪው አካል ትልቁ ምክር ቤት (Grosser Rat) (100 አባላት ሲኖሩት፣ እነሱም በየአራት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ)
  • ስራ አስፈጻሚ አካል፣ የመንግስት አስተዳደር ምክር ቤት (Regierungsrat) (7 አባላት ሲኖሩት፣ እነሱም በየአራት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ)
  • የዳኝነት አካል፣ በካንቶን ደረጃ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች (Gerichte) ይገኛሉ።

ባዝል ከተማን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት: የባዝል ከተማ የካንቶኑ ፓርላማ፣ አስተዳደርና እንዲሁም ፍርድ ቤቶቹ የባዝል ኮሚዩኖችን ጨምረው በሃላፊነት ያስተዳድራሉ። „ሪኸን“ና „ቤቲንገን“ ሁለቱ ኮሚዩኖች አንድ የጋራ የህግ አውጪ አካል (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ Einwohnerrat) እንዲሁም አንድ የስራ አስፈጻሚ አካል (የኮሚዩኖች ምክር ቤት፣ Gemeinderat). አላቸው። በፌደራል ደረጃ ህግ አውጪው አካል ሁለት ምክር ቤቶች አሉት: የብሄራዊ ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት (Nationalrat und Ständerat) ናቸው ። የብሄራዊ መንግስቱ (7 አባላት) ሲኖሩት ስሙም ፌደራላዊ ምክር ቤት (Bundesrat). ተብሎ ይጠራል። በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች አሉ። ለምሳሌ በካንቶን ፍርድ ቤቶች የተፈረዱ ውሳኔዎችን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደ የበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ይቻላል።

የዲሞክራሲ መብቶች

ስዊዘርላንዳውያን ድምጽ የመስጠትና የመመረጥ መብታቸው የተጠበቀ ነው። የፖለቲካ አካላትን በፌዴራል እንዲሁም በኮሚዩናቸውና በካንቶን ደረጃ ይመርጣሉ። ለምርጫም ቀርበውም መወዳደር ይችላሉ። በተጨማሪም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በሚመለከት ህዝቡ እንዲወስን ሪፈረንደም ይደረጋል። በዚህም ነዋሪዎች በኮሚዩናቸው፣ በካንቶናቸው እንዲሁም በፌደራል ደረጃ በሚያቀርቧቸው ሐሳቦች ላይ ድምጽ በመስጠት መወሰን ይችላሉ (በቀጥታ በዲሞክራሲ)። ይህንን ለማድረግ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት እንቅስቃሴ መጀመርና ማድረግ ይጠበቅበታል። በBasel-Stadt ካንቶን ነዋሪ የሆኑ የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በመምረጥና በህዝብ ውሳኔ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም። ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ጥያቄና አጀንዳ ካላቸው፣ ለአስተዳደሩ ጽ/ቤት ፊርማ አሰባስበው ማቅረብ ይችላሉ። ከዚህ ባለፈም በኮሚሽኖች፣ ጥቅም በሚያስጠብቁ ቡድኖች ወይም በማህበራቶች መደራጀትና መሳተፍ ይችላሉ።

መሰረታዊ መብቶች

የፌደራል ህገ መንግስቱ (Bundesverfassung) ከስዊዘርላንድ የሕግ መርሆዎች ሁሉ የበላይ ነው። የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ በአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ኮንቬንሽን (EMRK) ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እነዚህም ዋና አስፈላጊ የመሠረታዊ መብቶች አካል ናቸው። የሰው ልጅን በህይወት የመኖር መብት ይጠብቁለታል፣ ለምሳሌ ያክል የመኖር መብት ፣ወይም በችግር ግዜ እርዳታን የማግኘት መብቶን ይጨምራል። ከዚህም በተረፈ ግለሰቦችን ከመንግስታዊ የስልጣን ጥቃት ወይም አነስተኛ ግሩፖችን ከአብላጫው ለመጠበቅና ለመከላከል ያስችላል። ማንም ሰው ሌላውን በማንነቱ፣ በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጾታው ወይም በጾታዊ ዝንባሌው ምክንያት እንዳይገለል ዋስትና ይሰጣል። በዘረኝነት ምክንያት መገለል የሚደርስባቸው ሰዎች፣ በካንቶን Basel-Stadt ያለ ክፍያ እርዳታና ምክር ማግኘት ይችላሉ። በስዊዘርላንድ የሃይማኖት ነጻነት፣ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት ሰፍኗል።